Sunday, 1 November 2015

አስደንጋጩ የደቡብ ሱዳን ግምገማ

  ፓለቲካ - አስደንጋጩ የአፍሪካ ኅብረት የደቡብ ሱዳን ግምገማ

አስደንጋጩ የአፍሪካ ኅብረት የደቡብ ሱዳን ግምገማ ዋና ዜና
01 November 2015 ተጻፈ በ 
Source :- Ethiopian Reporter
Posted By : Abiy Abebe 

አስደንጋጩ የአፍሪካ ኅብረት የደቡብ ሱዳን ግምገማ

ደቡብ ሱዳን ራሷን የቻለች ሉዓላዊ አገር ሆና ብቅ ያለችው እ.ኤ.አ. በሐምሌ 2011 ነበር፡፡ ደቡብ ሱዳናውያን ይህን ነፃነት ለመቀዳጀት እ.ኤ.አ. ከ1956 ጀምሮ ከሰሜን ሱዳናውያን ጋር ጦርነት ውስጥ ቆይተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1977 በደቡብ ምዕራብ ሱዳን ነዳጅ መገኘቱ ከተረጋገጠ በኋላ፣
የእርስ በርስ ጦርነቱ ይበልጥ ተጧጡፎ ቀጠለ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1983 በኮሎኔል ጆን ጋራንግ አማካይነት የሱዳን ሕዝቦች ነፃ አውጭ ጦር መቋቋም ትግሉን ይበልጥ የተደራጀ አደረገው፡፡
ለግማሽ ክፍለ ዘመን በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ ለቆየችው ሱዳን እ.ኤ.አ. በግንቦት 2005 የተፈረመው ሁሉን አቀፍ የሰላም ስምምነት የለውጥ መሠረት ተደርጎ ተወስዶ ነበር፡፡ ይህ ስምምነት ደቡብ ሱዳን በስድስት ዓመታት ውስጥ ነፃ አገር የምትሆንበትን አካሄድም የነደፈ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት እ.ኤ.አ. ከጥር 9 እስከ ጥር 15 ቀን 2011 በተካሄደ ሕዝበ ውሳኔ ደቡብ ሱዳናውያኑ ነፃነታቸውን መረጡ፡፡
ነፃነቱ ከሱዳን መንግሥት ጋር የነበረውን አተካሮ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት በር የከፈተ ቢሆንም፣ ከጋራ ጠላታቸው ከካርቱም ጋር የተባበሩት የደቡብ ሱዳን ሕዝቦች የውስጥ ችግር ለማገርሸት ጥቂት ጊዜ ብቻ ነው የፈጀው፡፡ ይህ ልዩነት እየተባባሰ መጥቶ ነፃነቱ ያመጣዋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን ለውጥ እያጨለመው መጣ፡፡ ደቡብ ሱዳን ከነፃነትም በኋላ ከሱዳን ጋር ያላት ውጥረት የተለያየ ገጽታ እየያዘ ቢቀጥልም፣ በራሳቸው በደቡብ ሱዳናውያን መካከል የተከሰተው አለመግባባት ሌላ መጠነ ሰፊ ስቃይና መከራ ያስከትላል ብሎ የገመተ ብዙም አልነበረም፡፡
በደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና በምክትላቸው ዶ/ር ሪክ ማቻር መካከል ያለው ልዩነት ወይ ይፋ ጦርነት ያመራው እ.ኤ.አ. በታኅሳስ 2013 ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ የዶ/ር ማቻር ታማኝ ወታደር ናቸው ባሏቸው አካላት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተደርጎብኛል ማለታቸውም ይታወሳል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ በደቡብ ሱዳን መንግሥትና በተቃዋሚዎች መካከል በአዲስ አበባ እ.ኤ.አ. ከጥር 2014 ጀምሮ በተለያዩ ዙሮች ድርድሮች ቢካሄድም እስካሁንም ችግሩ ተባብሶ እንደቀጠለ ነው፡፡ በየጊዜው የሚፈረሙ የተኩስ አቁም ስምምነቶችም በሰዓታት ልዩነት መጣሳቸው ለደቡብ ሱዳን አዲስ ነገር መሆኑ አቁሟል፡፡
በዚህ ሁኔታ ውስጥ የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ደኅንነት ምክር ቤት እ.ኤ.አ. ታኅሳስ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. የደቡብ ሱዳንን ሁኔታ የሚመረምር ኮሚሽን እንዲቋቋም ወሰነ፡፡ ኮሚሽኑ በደቡብ ሱዳን ግጭት ወቅት የተከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ተገቢነት የሌላቸው ሌሎች ድርጊቶች እንዲመረምር፣ የጥሰቶቹን መነሻዎች እንዲለይ ግጭቶቹና ጥሰቶቹ ዳግም እንዳይከሰቱ በሚያስችል ሁኔታ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ፣ እርቅ መፍጠርና ጠባሳዎችን ለማዳን የሚያስችሉ ምክረ ሐሳቦችን እንዲሰጥና ደቡብ ሱዳንን ወደ አንድነት፣ ትብብርና ዘላቄ ልማት የሚወስዱ መንገዶችን እንዲጠቁም ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር፡፡
መጀመሪያ ላይ ኮሚሽኑ ሪፖርቱን በሦስት ወራት ውስጥ እንዲያስረክብ ተወስኖ ነበር፡፡ ይሁንና የተሰጠውን ኃላፊነት በሚገባ ለመወጣት የተሰጠው ጊዜና በጀት በቂ እንዳልሆነ የኮሚሽኑ ሰብሳቢ የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ቅሬታ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ በአጠቃላይ የኮሚሽኑ አባላት አምስት ሲሆኑ፣ ከኦባሳንጆ በተጨማሪ ዕውቁ ኡጋንዳዊ ተማራማሪ ማህሙድ ማምዳኒም ተካተዋል፡፡ ኮሚሽኑ የሪፖርቱ ጊዜ ከተራዘመለት በኋላ እ.ኤ.አ. በጥቅምት 15 ቀን 2014 ለአፍሪካ ኅብረት ያቀረበ ቢሆንም፣ ሪፖርቱ ይፋ ሳይደረግ ቆይቶ ከቀናት በፊት ይፋ ሆኗል፡፡
‹‹በሪፖርቱ የተካተቱትን ዝርዝርና አንገብጋቢ ጉዳዮች ካየን ለምን ተጨማሪ ጊዜ እንደወሰደ መገመት አይከብድም፡፡ ሪፖርቱ ጉዳዮችን በጥልቀትና በዝርዝር የዳሰሰ ሲሆን፣ በደቡብ ሱዳን ውስጥ ያሉና ከዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት አካላት ጋር ምክክር በማድረግ፣ በግጭቱ የተሳተፉ ተገዳዳሪ ወገኖችን በማሳተፍ፣ ፖለቲካዊ ስሱ የሆኑ ጉዳዮችን ያካተተ ከመሆኑ አንፃር ለምን ዘገየ የሚለው እንደ ጉዳይ ባይታይ እመርጣለሁ፤›› ያሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም መምህርና በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሰንዴይ ኦኬሎ ናቸው፡፡
ኮሚሽኑ እ.ኤ.አ. በመጋቢት 2014 ሥራውን ከጀመረ በኋላ ተከሰቱ የተባሉ ወንጀሎችንና የመብት ጥሰቶችን የመረመረ ሲሆን፣ በዚህም የዓይን እማኞችን ጨምሮ የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግሯል፡፡
በማስገደድ ሰው ሰውን እንዲበላ ማድረግና ሌሎች አሰቃቂ ድርጊቶች ተፈጽመዋል
የኮሚሽኑ ሪፖርት ከተጠናቀረ በኋላ የሁለቱ ወገኖች ግጭት ባለፉት 15 ወራት አለመቀዝቀዙን የሚጠቁሙ መረጃዎች ተሠራጭተዋል፡፡ ይሁንና በሪፖርቱ የተካተቱ የመብት ጥሰቶች ለብዙዎች እጅግ አስደንጋጭና እንቅልፍ የሚነሱ ሆነዋል፡፡ ሰዎች ተገደው ሰው እንዲበሉ መደረጋቸው የዓለም መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ የቡድን አስገድዶ መድፈር፣ በቁም በማቃጠል ግድያ መፈጸም፣ ግርፋትና ኢሰብዓዊ አያያዝ ከእነዚህ አሰቃቂ ድርጊቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ድርጊቶች በሁለቱም ወገኖች መፈጸማቸው በሪፖርቱ የተገለጸ ሲሆን፣ በአሥር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን ዜጎች መገደላቸውና ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከአገራቸው ለመሰደድ መገደዳቸውም ተመልክቷል፡፡
ለደቡብ ሱዳን ግጭት አዲስ ክስተት ባይሆንም የኮሚሽኑ አባላት ያነጋገሯቸው ደቡብ ሱዳናውያን በዚህ መጠንና ዓይነት የመብት ጥሰቶችን ከዚህ ቀደም ሲል አለመመልከታቸውን መግለጻቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ በተለይ ሰላማዊ ዜጎችን የጥቃት ሰለባ ማድረግ አዲስ ክስተት እንደሆነ መናገራቸውም ተጠቅሷል፡፡
በሁለቱም ወገኖች በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ተመሳሳይ ድርጊቶች መፈጸማቸውን የዘረዘረው ሪፖርቱ፣ በተለይ በጉደሌ እ.ኤ.አ. ታኅሳስ 16 ቀን 2013 የተፈጸመው ድርጊት የግጭቱን ገጽታ በሚገባ የሚያሳይ እንደሆነ አመልክቷል፡፡ በዚያች ዕለት የሳልቫ ኪር ወታደሮች ዶ/ር ማቻርን ይደግፋሉ የተባሉትን የኑዌር ብሔር አባላትን በማስገደድ የሰው ደም እንዲጠጡ፣ የሰው ሥጋ እንዲበሉና ወደሚንበለበል እሳት ተወርውረው እንዲገቡ በማድረግ ማስገደላቸውን ከዓይን እማኞች ማረጋገጡን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ የሁለቱ ወገኖች ጦር ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግን መጣሱንም አካቷል፡፡ ጥቃቱ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ከማተኮሩ በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያናት፣ መስጊዶች፣ ሆስፒታሎችና ከተሞች መውደማቸውንና የሰብዓዊ ዕርዳታዎች መስተጓጎላቸውን፣ እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት እንዲሳተፉ መደረጋቸውንም አብራርቷል፡፡
ከእነዚህ ድርጊቶች አንፃር የጦር ወንጀሎችና በሰብዓዊነት ላይ የሚቃጡ ወንጀሎች መፈጸማቸውን መደምደም እንደሚቻልም አመልክቷል፡፡ ይሁንና በግጭቱ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል ለማለት ኮሚሽኑ በቂ መረጃና ምክንያት አለማግኘቱን አስገንዝቧል፡፡
ከአጠቃላይ ሁኔታዎች ለመረዳት እንደሚቻለው የተከሰቱት ጥሰቶች በተቀናጀ ሁኔታ የተከናወኑ በመሆናቸው፣ ሰላማዊ ግለሰቦችን በብሔራቸው ወይም በፖለቲካ አቋማቸው  የተነሳ ጥቃት እንዲደርስባቸው የማድረግ ፖሊሲን መንግሥት ተከትሏል ብሎ መደምደም እንደሚቻልም ኮሚሽኑ አመልክቷል፡፡
ተጠያቂነትን ማረጋገጥ
ኮሚሽኑ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂነትን እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል በሚለው ጉዳይ ላይ ቅድሚያ ለደቡብ ሱዳን ሕዝቦች በመስጠት መመርመሩን ገልጿል፡፡ በዚህም ተጠያቂነትን ማረጋገጥ የሚቻለው ሰላምን ሳያደፈርሱና ለደቡብ ሱዳን አዲስ ጅማሮ አረጋግጦ መሆን እንዳለበት አስተያየት ከአብዛኛው ዜጋ እንደተሰጠው አመልክቷል፡፡
ይህ ማለት ድርጊቶችን የፈጸሙ ግለሰቦች ተጠያቂ አይሁኑ ማለት እንዳልሆነ ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡ በደቡብ ሱዳን የገነነውን ከተጠያቂነት የማምለጥ ባህል እንዲገረሰስ የሕዝቡ ፍላጐት እንደሆነ አመልክቷል፡፡ ይሁንና ይህ የወንጀል ተጠያቂነት ዕርቅንና ዘላቂ ሰላምን ሳይገፋ መከናወን እንዳለበት አስገንዝቧል፡፡ በሁለቱም ወገኖች ያሉ አብዛኛዎቹ በኮሚሽኑ አባላት የተጠየቁ ዜጐች በግለሰብ ደረጃ ፕሬዚዳንቶች ሳልቫ ኪርና ተቀናቃኛቸው ዶ/ር ሪክ ማቻር ለተከሰተው ቀውስ፣ ለመባባሱና ለደረሰው የመብት ጥሰት ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው መናገራቸውም ተጠቅሷል፡፡ ምን ዓይነት ተጠያቂነት የሚለው ከተሰጡት ምላሾች መረዳት ባይቻልም የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔርና የፖለቲካ ወይም አስተዳደራዊ ተጠያቂነትን በማቀላቀል መጠቀም እንደሚቻል ኮሚሽኑ መክሯል፡፡
መላሾቹ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በተለይ ከፍተኛ የፖለቲካና የወታደራዊ መሪዎችን በተመለከተ በብሔራዊ የፖለቲካና የፍትሕ ተቋማት ላይ መተማመን የሌላቸው በመሆኑ በአፍሪካ የሚመራ፣ በአፍሪካውያን ባለቤትነት የሚካሄድና በአፍሪካ ሀብትና የሕግ ማዕቀፍ የሚመራ፣ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚታገዝና የደቡብ ሱዳን ዳኞችና ጠበቆች የሚሳተፉበት አሠራር ተግባራዊ እንዲሆን ምክረ ሐሳብ ሰጥቷል፡፡
ኮሚሽኑ ከፍትሕና ከዕርቅ ቅድሚያ ለየቱ ይሰጥ የሚለው ጥያቄ በውጥረት የተሞላ መሆኑን አስታውሶ፣ ለደቡብ ሱዳን ችግር መፍትሔ ለመስጠት የእያንዳንዱን ችግር ዓውድ በማጥናት የተለያዩ መፍትሔዎችን በመቀላቀል መጠቀም እንደሚችል አመልክተዋል፡፡ የዚህ ሒደት መጀመር ያለበት የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ቀያቸው በመመለስ መሆን እንዳለበትም አስገንዝቧል፡፡
ኮሚሽኑ ችግሩን ለዘለቄታው ለመቅረፍ የእውነትና የዕርቅ ኮሚሽን መቋቋም እንዳለበትም ሐሳብ አቅርቧል፡፡ የሚቋቋመው ኮሚሽን ወደፊት በሚደረጉ ምክክሮች በሚወሰነው ጊዜ ውስጥ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን በማጣራት እውነት እንዲወጣ፣ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲመጣ፣ ይቅር ባይነት እንዲኖር፣ ተጠቂዎችን ወደ ቦታቸው ለመመለስ ጥሪ እንዲደረግ በመሥራት ፍትሕና ዘላቂ ዕርቅ እንዲፈጠር ማድረግ እንዳለበት ምክረ ሐሳቡ ያብራራል፡፡
ከኮሚሽኑ አባላት መካከል ፕሮፌሰር ማሕሙድ ማምዳኒ በጻፉት የተለየ አስተያየት፣ ፍትሕንና ዕርቅን ለመቀላቀል ተግባራዊ ለማድረግ አራት ወሳኝ ጉዳዮች ግንዛቤ ውስጥ ሊገቡ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ እነዚህም ከተጠያቂነት የማምለጥ ባህል፣ የተጠያቂነትን ትርጉም መረዳት፣ የፖለቲካዊ ሒደት አስፈላጊነትን መረዳትና የወንጀል ፍትሕ አስተዳደርን እንዴትና መቼ እንጠቀማለን? የሚለውን መለየት ናቸው፡፡
ፕሮፌሰር ማምዳኒ አይሲሲን መሰል ተቋማት የሚከተሉት የምዕራባውያን የፍትሕ አረዳድ ለአፍሪካ አዋጭ አይደለም ብለው ከሚከራከሩ ምሁራን አንዱ ናቸው፡፡ በዚህም አስተያየታቸው ‹‹አፍሪካዊ መፍትሔ›› ያሉትን አካሄድ ሲያብራሩ ምዕራባውያን የእኛ መፍትሔ የትም የሚሠራ ነው፣ ለሁሉም የሚስማማ ነው በማለት ያደረሱትን ጥፋት በመዘርዘር ነው፡፡ ምዕራባውያኑ ደቡብ ሱዳን ከነፃነቷ በፊት ራሷን የማስተዳደር ታሪክ እንደሌላትና የተፈተኑ ተቋማት እንደሌላት እየታወቀ ‹‹ምርጥ ተሞክሮዎች›› በመቅዳት ደቡብ ሱዳንን ለመገንባት መሞከር የዚህ ችግር ማሳያ አድርገው አቅርበዋል፡፡ ከተጠያቂነት አንፃር ወንጀል ከተፈጸመ አጥፊውን መቅጣት ነው በሚል ጉዳዮችን የወንጀልና የቅጣት ጉዳይ አድርገው አቅለው እንደሚመለከቱም አመልከተዋል፡፡
ድጋፍና ተቃውሞዎች
‹‹ይህ ሪፖርት ከአፍሪካ ኅብረት ከመምጣቱ አንፃር ታሪካዊ የሚባል ነው፡፡ መሰል ሪፖርቶችን የምናገኘው ከሒውማን ራይትስ ዎች፣ ከአምነስቲ ኢንተርናሽናልና መሰል ተቋማት ነበር፡፡ ሪፖርቱ በጣም ሸንቋጭና ጥፋቶችን በግልጽ የሚዘረዝር መሆኑ የተለየ ያደርገዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች ለደረሰው ጭፍጨፋ የሞራል ከተቻለም የወንጀል ተጠያቂነትን ለሰላም ሲሉ መቀበል አለባቸው፡፡ ይሁንና የደረሰው ጭፈጨፋ ደረጃ ተጨማሪ ማብራሪያ የሚጠይቅ ነው፤›› በማለት ለሪፖርተር በጽሑፍ አስተያየታቸውን የሰጡት መቀመጫቸውን አሜሪካ ያደረጉት የሰላምና ደኅንነት ተንታኝና ተመራማሪ  አቶ ዓለማየሁ ፈንታው ናቸው፡፡
በተመሳሳይ ዶ/ር ሰንዴይ ሪፖርቱ አስደንጋጭ የሆኑ ግኝቶችን ጨምሮ የተለያዩ ጉዳዮችን በጥልቀትና በስፋት በመዳሰስ፣ ግልጽ ማብራሪያ በመስጠትና ምከረ ሐሳብ በመስጠት ሕያው ሰነድ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አፍሪካ ኅብረት ከሚከተለው መርህና የሥነ ምግባር ደንብ አኳያ ጉዳዩን መመርመሩንም አመልክተዋል፡፡ ‹‹የችግሩን መነሻ፣ የተከሰተው ነገር ምን እንደሆነ? መፍትሔው ምን እንደሆነ? በዝርዝርና በግልጽ ያስቀመጠ ሪፖርት ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረትም ሆነ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ምን ማድረግ እንዳለባቸው አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ የተከሰተው ነገር ድጋሚ እንዳይከሰት ምን መደረግ አለበት? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የሚረዳ ነው፡፡ ሰነዱን በሚገባ በመመርመርና በመፈተሽ የመፍትሔው አካል መሆን እንጂ ስሜታዊ በመሆን ለሌላ በቀል የሚጋብዘን መሆን የለበትም፤›› ብለዋል፡፡
ሪፖርቱ በደቡብ ሱዳንም የተለያዩ የድጋፍና የተቃውሞ አስተዳደሮችን እያስተናገደ ነው፡፡ ጥቅምት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ሪፖርቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ የደቡብ ሱዳን የሰብዓዊ መብት ውትወታ ማኅበረሰብ ባወጣው መግለጫ፣ ሪፖርቱ በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማምጣት ወሳኝ ነው ብሏል፡፡ ‹‹የተከሰቱትን ጭፍጨፋዎች የሚያጋልጥ በመሆኑ ክህደትና መነቃቀፍ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ለተፈረመው የሰላም ስምምነት መፈጸም የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል፤›› ብሏል፡፡
በተመሳሳይ ዘ ኮሙዩኒቲ ኢምፓወርመንት ፎር ፕሮግረስ ኦርጋናይዜሽን የተባለው ሲቪል ማኅበር፣ ሪፖርቱ የአፍሪካ ኅብረት ለፍትሕ የሚሠራ ተቋም መሆኑን የሚያሳይ ታሪካዊ ሰነድ እንደሆነ ገልጿል፡፡ የማኅበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኤድመንድ ያካኒ ሁለቱ ወገኖች በሪፖርቱ ለቀረባቸው ወቀሳ ምላሽ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሪፖርቱ ቅሬታ የቀረበባቸውና ተጠያቂ የተደረጉት ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የፀጥታ ጉዳዮች አማካሪ ቱት ጋትልዋክ ሪፖርቱን ‹‹መሠረተ ቢስ›› ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ በተለይ የደቡብ ሱዳን የፀጥታ ኃይሎች በኑዌር ብሔር አባላት ላይ ጥቃት የፈጸሙት በመንግሥት ፖሊሲ ነው መባሉ እውነትነት የሌለው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሪፖርቱ ከሰብዓዊ መብት ጥሰትና ከተጠያቂነት በተጨማሪ በ315 ገጾች በተቋማት ይዞታ ላይ፣ በአስተዳደር ሥርዓቱ በተለይ በፌዴራል የመንግሥት መዋቅሩ ላይ፣ በፀጥታ ዘርፍና በፖሊስ ላይ፣ በፋይናንስ አስተዳደር ላይ፣ በፍትሕ አስተዳደር ሥርዓቱ ላይ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በሲቪል ማኅበራትና በሚዲያ ሚና ላይ ጥልቅ የሆነ ትንተና ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡
በርካታ ተንታኞች በሪፖርቱ አቀራረብና ይዘት ላይ ቅሬታ የሌላቸው ሲሆን፣ የደቡብ ሱዳንን ችግር ለመቅረፍ መቼና እንዴት ጥቅም ላይ ይውላል? በሚለው ላይ ግን ያላቸውን ጥርጣሬ አስፍረዋል፡፡
Source :- Ethiopian Reporter
Posted By : Abiy Abebe

No comments:

Post a Comment