Tuesday, 14 July 2015

የፖለቲካ ሽሙጥ በ Andualem Buketo Geda / አብይ 1702



          Andualem Buketo Geda


       ፖላንድ ዛሬ ምን እንደነካዉ ባያዉቅም በጥዋት ቁልት አድርጎታል፡፡
እስቲ ከሰፈር ልዉጣ እና ወክ ላድርግ አለ፡፡ተወልዶ ካደገበት ሰፈር ቁልቀል ወደ ታች እጁን ኪሱ ከቶና አንገቱን ደፍቶ በቀስታ መራመድ ጀመረ፡፡
እታች ሰፈር መአት ሀገራት ተሰብስበዉ ይንጫጫሉ፡፡አንዳንዶቹን በአይን ብቻ ነዉ የሚያዉቃቸዉ፡፡ ጠጋ ብሎ የሚጨቃጨቁትን ሲሰማ የሆነች ግሪክ የምትባል ችስታ እቁብ በልታ ስታበቃ ለሌሎቹ ተራ አልከፍልም በማለቷ የተነሳ ዉዝግብ ነዉ፡፡
ከፖላንድ ጋር አብሮ የተማረዉ አቶ ጀርመን ከሁሉም በላይ እየቀወጠዉ ነዉ፡፡
ግሪክ “ወ..ይ…ንሽት እቴ! የፈለገ ቢሆን አልከፍልም በቃ ቸግሮኛል ቸግሮኛል አትጨቅጭቁኝ“ እያለች ወገቧን ይዛ ትዉረገረጋለች፡፡(በዛ ላይ በጥዋት ይሄንን ወይን እንደጉድ ቀማምሳለች)
“ እንዴት አትከፍይም ባለፈዉ የሌላ ሰዉ እጣ ሁላ በልተሸ የለ እንዴ!? ተይ ግሪክ ተይ ሰዉ ይታዘብሻል! አበስገበርኩ!“ አለቻት ፈረንሳይ ፡፡የተቀባችዉ ሽቶ ይገርማል፡፡
“አሁን ምንም የለሽም የምር?“ አለቻት ጣልያን
“እመበቴን! እዉነቴን ነዉ ቤሳቤስቲን የለኝም“ ብላ መዳፏን በመሃላ ግጥም አድርጋ መታቻት፡፡
ግሪክ ኦርቶዶክስ ስለሆነች እመቤቴን ካለች ሁሉም እንደማትዋሽ ያዉቃሉ በዛ ላይ ጣልያን የማሪያም ነገር አይሆንላትም በአንዴ አመነቻት፡፡
ፖላንድ ዳር ላይ ቆም ብሎ ሁኔታቸዉን በግርምታ ሲከታተል ቆይቶ እየሳቀ ጥሏቸዉ ሄደ ፡፡የገረመዉ ነገር የግሪክ ድርቅናን ላየ ተበዳሪ ሳትሆን አበዳሪ መምሰሏ ነበር፡፡ ለምን እንደሆነ ባያዉቅም ዛሬ ያማረዉ ጥቁር ቺክ መጥበስ ነበር
የሜድትራኒያንን መስመር ተከትሎ ጥላ ጥላዉን ወደ ታች ወረደ፡፡በዛ ያሉ ሙስሊሞች ወንዶችም ሴቶችም የተሰበሰቡበትን ሰፈር በስተግራዉ ትቶ ወደ ታች ወረደ፡፡የጾም ወቅት ስለሆነ አካባቢዉ ጭር ብሏል፡፡
በኤደን(አደን) ባህረስላጤ አድርጎ ወደ አፍሪካ ለመሻገር ጠባቧን ባበል መንደብ እንጣጥ ብሎ ተሻገረ እና ሞቅ ደመቅ ወዳለዉ የቺኮች ሰፈር ገባ፡፡
መጀመሪያ ያጋጠመችዉ ኤርትራ የምትባል ፍንዳታ ቺክ ነበረች፡፡ሳታድግ ያደገች የሆነች ነገረኛ ሆነችበት፡፡ፊቷ በጸብ ብዛት ተቦጫጭሯል፡፡ ሰላምታ ሰቷት ትንሽ ሲያዋራት እንዲሁ ቁጣ ቁጣ እንደሚላት ገባዉ፡፡
“ሻይ ቡና እንበል?!“ አላትና እሺ ስትለዉ አረፍ የሚሉበት ቦታ ፍለጋ ወደ ታች የቀይ ባህርን ዳርቻ ተከትለዉ ወረዱ፡፡
እንደነገረችዉ ከሆነ እድሜዋ ገና ሃያዎቹ መጀመሪያ ነዉ፡፡ ፖላንድ ልጅነቷ ቢመቸዉም ነገረ ስረዋ ግን እንደአርባ አመት ነገረኛ ባልቴት ሆነበት ፡፡ ኮንፊደንስ የላትም፡፡ ዝም ብላ ከጎን ከጎኑ እየሄደች ሃላፊ አግዳሚዉን ትገላምጣለች፡፡
ትንሸ ወረድ እንዳሉ የሆነች አጭር ድቡልቡል ሴትዮ አጠገብ እንደደረሱ ኤርትራ ከመሬት ተነስታ
..
“ቆይ ጠብቂኝ አንቺ ኩሩሩ አገኝሻለሁ! ፈረንሳይ የምታድንሽ መስሎሻል!“
አለች ሌባ ጣቷን እያወዛወዘች

“አሁን ምን አደረኩሽ እስቲ?“ አለች ጅቡቲ ብዙም ፍርሃት አይታይባትም፡፡
“ከዛች ሸርሙጣ አሮጊት ጋር አፍለአፍ ገጥመሽ ያላየሁሽ እንዳይመስለሽ!“ አለቻት ኤርትራ ፡፡
“ቆይ ከጎረቤቴ ጋር ቡና መጠጣትም ልትከለክይኝ ነዉ?“ አለች ጅቡቲ እየተሳቀቀች በአንድ በኩል ይሄ ደግሞ የማነዉ ሸበላ በሚል ፖላንድን ከእግር እስከራሱ እየገረመመች፡፡
“አሳይሻለሁ ቀንሽን ጠብቂ!“ አለችና መንገድ ዳር ቆሞ የሚጠብቃት ፖላንድ ጋር ለመድረስ ራመድ ራመድ አለች፡፡
“አስቆምኩህ አይደል ይቅርታ!“ አለችዉ እንደደረስች፡፡

“አይ ምንም አይደል“ አለ ፖላንድ፡፡ እንደእዉነቱ ከሆነ ይህቺን ነገረኛ ፍንዳታ ጥሎ ለመሄድ ወስኗል፡፡መልኳ እንኳን አሪፍ ነበር ጠባይ ግን …!.እግዚያብሄር መቼም ሁሉን አይሰጥ፡፡

“ተጫወች“ አላት ዝም ስትል፡፡ ዞር ብሎ መልኳን ሊያያት ካቀረቀረበት ቀና ሲል ከሆነች ሙስሊም ጋር ስትዛዛት ያዛት፡፡

“ደሞ ይህቺ ምን አደረገችሽ?!“ አላት፡፡

“የመን? ምን ያላደረገችኝ ነገር አለ? ቆይ እስራላታለሁ“ አለች፡፡
“ አረ እቺስ ከፈሷ የተጣላች ነች“ አለፖላንድ በሆዱ፡፡ ካለ እሰራላታለሁ ምንም ወሬ የላትም፡፡
ጥሩ ካፌ እያፈላለጉ ወደ ታች በአሸዋዉ ቁልቁል ሲጓዙ ኤርትራ ቁርጥ እሷን የምትመስል ሴትዮ ስታይ ድንግጥ ብላ ቆም አለች፡፡
ፖላንድ ሰረቅ አድርጎ አያት፡፡ፊቷ ልዉጥዉጥ ብሏል፡፡እጇና እግሯ ላይ ያደረገቻቸዉን ጌጦች አወለቀች፡፡
“ምነዉ? ያምርብሻል እኮ ጌጦችሽን አታዉልቂያቸዉ“ አላት፡፡ በተለይ እግሯ ላይ ያደረገችዉ ጌጥ ያምራል፡፡

“ምንድነዉ ይሄ?“ አላት የእግሯን ጌጥ እየጠቆመ
“ አሰብ ወደብ ይባላል“፡፡ አለችዉና ወደቡን አዉልቃ ኪሷ ዉስጥ ከተተችዉ፡፡

“እና ለምን ታወልቂዋለሽ?“ አላት፡፡

“ምን እባክህ የእራሴ አይደለም፡፡ ከታች የምትመጣዉን አየሃት? ማዘር ነች ኢትዮጲያ ትባላለች የእሷ ነዉ“፡፡አለችዉ እየተሸማቀቀች፡፡
ግልጽነቷን ወደደላት፡፡
“እና አሰቡን አዉሳሽ ነዉ? አላት ፖላንድ ፡፡
“ አረ አይደለም !ማዘር አንድ መለስ የሚባል ልጅ ነበራት እሱ ነዉ ከቤት አዉጥቶ የሰጠኝ፡፡ “ማዘር ምን ይሰራላታል…. ግመል መጠጫ ምናምን..“ ብሎ ነዉ የሰጠኝ ብቻ ያኔ የተናገረዉ አልገባኝም ዉሰጂዉ አለኝ፡፡ እኔ ደግሞ እሷም የምታዉቅ መስሎኝ ግርግድ አድርጌ ገበያ ብቅ ስል ለካ ማዘር የሆኑ ነገረኛ ነገረኛ አማራ ኦሮሞ ጉራጌ ትግሬ ምናምን የሚባሉ ልጆች አሏት ፡ መንገድ ላይ አግኝተዉኝ ሊገሉኝ !!በተለይ አማራ የሚባለዉ ልጇ እንዴት ነገረኛ እንደሆነ አትጠይቀኝ …“አረ ባክህ ወንድምህን ጠይቀዉ ሰርቄ አይደለም የወሰድኩት እራሱ ነዉ የሰጠኝ“ ብለዉ አንገቴን ይዞ በአደባባይ አዉልቂ አይለኝም….ሆ ሆ ይ…“ አለች
ኤርትራ ከፖላንድ ጋር እያወራች በአይኗ የኢትዮጲያን እንቅስቃሴ በጥንቃቄ ትከታተላለች፡፡ ኢትዮጲያ ከታች በኩል መንገድ ዳር ከኬንያ ጋ የሆነ ወሬ ይዛ ቆማለች፡፡
ባለፈዉ ለማይረባ ባድመ ለሚባል የማዘር ባርኔጣ ልጆቿ ቀጥቅጠዉ ሊገሉኝ ነበር በእናትህ! ያ መለስ ነዉ ያኔም ያዳነኝ ፡፡መቼም እግዚያብሄር ይስጠዉ !አንዳንዴማ የወለድኩት ልጄ ነዉ የሚመስለኝ ፡በሁለት እግሬስ ያቆመኝ እሱ አይደል! አይ ለእኔ ያለዉ አመለካከት! ብቻ ነፍሱን ይማረዉ፡፡ ጥሩ ሰዉ አይበረክትም ባፈዉ በሞት ተለየን“ አለችና እንባዋን አበስ አደረገች፡፡
ፖላንድ ኤርትራን ማዳመጥ ትቷል፡፡ አዲሷ ሴትዮ (ኢትዮጲያ) ቀልቡን ገዝታዋለች፡፡
ኤርትራም ኢትዮጲያን ካየች በኋላ ከፖላንድ ጋር መቆየት አልፈለገችም፡፡ በቃ ደዉልልኝ አለችዉና የዉሸት ስልክ ሰጥታዉ ከሁሉም ጋር እየተሰዳደበች በመጣችበት አቅጣጫ ተመልሳ ጥድፍ ጥድፍ እያለች ተመለሰች፡፡
ፖላንድ ኮቱን አስተካከለና በኩራት እየተራመደ ወደቆንጆዋ ሴትዮ ቀረበ፡፡
“ ጤና ይስጥልኝ ፖላንድ እባላለሁ“ አላት፡፡

“ኢትዮጲያ“ አለችዉ፡፡ አቤት ድምጿ ሲያምር፡፡ ፖላንድ ደነገጠ፡፡
“ስለተዋወኩሽ ደስ ብሎኛል“ አላት፡፡

“ምንም አይደል“ አለችዉ፡፡
“እኔም ደስ ብሎኛል“ የምትለዉ መስሎት ነበር፡፡ ኩራተኛ ነገር ሳትሆን አትቀርም ብሎ አሰበ፡፡ ኮንፊደንሷ ከነጭ ጋር የምታወራም አትመስልም፡፡
“ወክ እንብላ?“ አላት ፡፡
እሺ ብላዉ ወደ ታች የምስራቅ አፍሪካን ቀንድ(HA) ተከትለዉ ወረዱ፡፡
የሆነች ሶማሊያ የምትባል የድሮ ቆንጆ ጋር ደረሱ፡፡

“ምን እንደዉ ይህቺ ሀገር በጠበጠችን እኮ!“ አለች ኢትዮጲያ ከባህሩ ዳር አሳ የምታጠምደዉን ሶማሊያ እየጠቆመች፡፡
“እንዴት?“ አላት በጎን ሰረቅ አድርጎ ኢትዮጲያን አያት፡ እንዴት አባቷ ታምራለች የድሃ ቆንጆ ናት አለ በልቡ፡፡
“ይኸዉ ልጆቿን በአግባቡ አትይዝ በዚ በኩል ባህሩ ላይ ይሄንን ህዝብ ይዘርፉታል! የየብሱን እንኳን እኔም አንዳንዴ ስራ ስፈታ ቤቷ እየሄድኩ ልክ አስገባላታለሁ የባህሩን ግን አልቻልኩም እድሜ ለዛ ልጅ የባህር በሬን አንስቶ ለዛች ለተረገመች ዲቃላ ልጄ ሰጣት፡ ምን እንዳስነካችዉ እኮ ነዉየሚገርመኝ ሰዉ በእናቱ እንደዚህ ይጨክናል?!“ አለችና በትካዜ አንገቷን ደፋች ፡፡
ሶማሊያ ጋር ስትደርስ “አሰላማለይኩም“ አለቻት በፈገግታ፡፡

“ሰለማ ለይኩም“ አጸፋዉን በትህትና መለሰች ሶማሊያ፡፡
“ስምሽ ግን ደስ ይላል“አለ ፖላንድ አትዮጲያን ሰረቅ አድርጎ እያያት ፡፡
“ በነገራችን ላይ የትምህርት ቤት ስሜ “የኢትዮጲያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ“ ነዉ ጓደኞቼ “ኢፌድሪ“ ነዉ የሚሉኝ“ አለችዉ፡፡
“የአባትሽ ስም ዲሞክራሲ ነዉ ወይስ ዲሞክራሲያዊ ስለሆንሽ ነዉ?“ አላት፡፡
“አረ ዲሞክራሲያዊ ስለሆንኩ ነዉ፡ የአባቴ ስም አይደለም፡፡“ አለችና ድንገት ትዝ እንዳለት ሁሉ ዉይ በናትህ እረስቼዉ ነዉ፡ ዛሬ የአለም የፋይናንስ ምናምን(እኔ እንኳን ፋይናንስ ስለሌለኝ ስሙ አይያዝልኝም አለችና ተሸኮረመመች)የሚባል ማህበር እኔ ቤት ነዉ ድግሱ፡፡ ሀገራት ሁሉ ቤት ተሰብስበዋል ቅር ካላለህ ሌላ ቀን እንገናኝ አለችዉና ስልኳን ሰጥታዉ እየሮጠች ሄደች፡፡
ከኋላዋ አያት ፡፡“እንዴት ታምራለች!“ አለ ፖላንድ ሳያስበዉ ለራሱ ጮክ ብሎ፡፡
ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ ፖላንድ ፍቅር ይዞታል፡፡ ገና እንደገባ ኢትዮጲያን ፌስ ቡክ ላይ በስሟ ፈልጎ አገኛት፡፡
ፕፋይል ፒክቸሯና ስለራሷ የጻፈችዉ እጅግ የተጋነነ ነዉ፡፡ያልሰራችዉን ግድብና ባቡር ከሆነ ጥልፍልፍ መንገድ ጋር ፕሮፋይል ፒክቸር ብላ ለጥፋለች፡፡
“ አይ ቺኮች እና ፌስ ቡክ!“ አለ ፖላንድ፡፡
ታይም ላይኗ ላይ ገባ ፡፡ እልም ያለች ጸረ ፕሬስ እና ጸረ ጋዜጠኛ ነች፡፡
“ወይ ዲሞክራሲ!“ አለ፡፡
የጋብቻ ሁኔታ አየ፡ ያላገባ ይላል ፡፡ ደስ አለዉ ፡፡ ከዚህ ቀደም አንድ የእሱ ሰፈር ነጭ ሊደፍራት ሞክሮ አዋርዳዋለች፡፡ጀግንነትስ ጀግና ናት አለ፡፡
ምርጫዋን አየ፡፡ “አንድ ልጇ መቶ ፐርሰንት አሽንፏል“ ይላል ፡፡ በሃአንደኛዉ ክ/ዘመን እንደዚህ አይነት ፋራ አለ አለና ሳቅ አለ፡፡
“ሞር“ የሚለዉን ተጫነዉ፡፡ ይሄዉ ልጅ 99 ፐርሰንት አሽንፏል ይላል፡፡ 2005 የሚለዉን ተጫነዉ፡፡ ይሄዉ ልጅ አሽንፏል እንደዉም የተወዳደሩት ወንድሞቹን የሞት ፍርድ አስፈርዶባቸዉ ከሀገር አባሯቸዋል፡፡
እንዴት ስሟ ኢፌድሪ ሆነ? ወይስ “ኢፌሪ“ ነዉ ያለችኝ? የዉሸት ስሟ ነዉ ማለት ነዉ …ፖላንድ ቅር አለዉ፡፡ ሊደዉልላት አሰበና ግራ ገባዉ፡፡
ይደዉል እና ምሳ ይብሉ?
ይመቻችሁ

No comments:

Post a Comment